ዶናልድ ትራምፕ በአባይ ጉዳይ ዛሬም የካይሮ ጠበቃ ሆነው ተከስተዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ያልተሳካላቸውን የእጅ ጥምዘዛ ካርድ ጊዜ ጠብቀው መዘውታል። ትራምፕ ተቋርጦ የቆየውን የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ድርድር ለማስጀመር፣ ለግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ በጻፉት ደብዳቤ ፍላጓታቸውን ገልጸዋል።
ትራምፕ በመጀመሪያ ዙር የሥልጣን ዘመናቸው በቀጥታ ወደ ነጩ ቤተመንግሥት ተጎትተው ባስገቡት ድርድር፣ ያጡትን ውጤት በሁለተኛው የሥልጣን ዘመናቸው ለማሳካት በድጋሚ ካርድ መዘዋል። በመጀመሪያ ዙር የአደራዳሪነት ሚናቸው ለግብፅ ውግንና በማሳየት 'ግድቡን ታፈነዳዋለች' በሚለው ንግግራቸው የሚታወቁት ትራምፕ፣ ዛሬም ለካይሮ ያላቸውን ውግንና በደብዳቤያቸው አንጸባርቀዋል።
ትራምፕ ለግብፁ ፕሬዜዳንት በጻፉት ደብዳቤ "ባለን የግል ወዳጅነት መንፈስ እና አሜሪካ ለግብፅ ሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት ባላት ቁርጠኝነት፣ በግብፅ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን 'የአባይን ውሃ መጋራት' ጥያቄ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በኃላፊነት መንፈስ ለመፍታት አደራዳሪነቷን ዳግም ለመጀመር ዝግጁ ነኝ " ብለዋል። አክለውም "በቀጠና የትኛውም አገር የአባይን ውድ ሃብት በተናጠል መቆጣጠር እና በሂደቱ ጎረቤቶቹን መበደል የለበትም" በማለት፣ ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ ጫና የመፍጠር በተደጋጋሚ የምትንጸባርቀውን አቋም ተጋርተዋል።
ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባጋሩት በዚህ ደብዳቤ ላይ "ቡድኔ እና እኔ የአባይ ወንዝ ለግብፅ እና ለሕዝቧ ያለውን ጥቅም እንረዳለን" ብለዋል። ይህ የትራምፕ አድሎ የተጫነው አቋም አስጀምረዋለሁ በሚሉት ድርድር ላይ በግልፅ እንደሚንጸባረቅ ከወዲሁ አመላካች ሆኗል።
ትራምፕ በደብዳቤያቸው ላይ "ትክክለኛ በሆነ ቴክኒካዊ ዕውቀት፣ ፍትሃዊ እና ግልጽ ድርድር እንዲሁም አሜሪካ በሚኖራት ጠንካራ የቁጥጥር እና የማስተባበር ሚና ከሁሉም የአባይ ተፋሰስ አገራት ጋር ዘላቂ ስምምነት ላይ መድረስ እንደምንችል አምናለሁ" ሲሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
አክለውም "በድርቅ እና ለረጅም ጊዜ በተራዘመ ደረቅ ዓመታት ወቅት ለግብፅ እና ለሱዳን ሊገመት የሚችል ውሃ እንዲለቀቅ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል እንድታመነጭ ያስችላል፣ የተወሰነውም ለግብፅ እና ለሱዳን ሊቀርብ ወይም ሊሸጥ ይችላሉ" ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የሕዳሴው ግድብ አለመግባባት ዘላቂ ከሆነ ቀጠናዊ መረጋጋት ጋር በተያያዘ "ከፍተኛ ትኩረት" የሚሰጡት ጉዳይ መሆኑን በደብዳቤያቸው ላይ ጠቅሰዋል። "ለመካከለኛው ምሥራቅ እና ለአፍሪካ ዘላቂ ሰላም ስሠራ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የተፈጠረውን አለመግባባት መፍታት ቁልፍ አጀንዳዬ ነው" ብለዋል።
ለፕሬዚዳንት አልሲሲ የተጻፈው ይህ ደብዳቤ ለኢትዮጵያው ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣ ለሱዳኑ አብደል ፈታህ አል ቡርሃን እንዲሁም በቀጠናው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ላላቸው የሳዑዲው ልዑል ሞሐመድ ቢን ሰልማን እና የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ቢን ዛይድ ተልኳል። የኢትዮጵያ የተላከው ደብዳቤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ልይቅ ከፕሮቶኮል የዘለለ የጎላ የውሳኔ ሥልጣን ለሌላቸው ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ስላሴ መላኩም ሌላ ጥያቄ አጭሯል።
የትራምፕ አቋም ለግብፅ በጉጉት ሰትጠብቀው የነበረ በመሆኑ በደስታ እንደምትቀበለው የሀገሪቱ መንግሥታዊ ጋዜጦች ከወዲሁ እያስነበቡ ነው። መንግሥታዊው አል አህራም ጋዜጣ በፕሬዝዳንቱ ደብዳቤ ላይ የሰፈረው የቋንቋ አጠቃቀም የግብፅን አቋም የሚደግፍ እንደሆነ ተደርጎ ሊተረጎም ይችላል ሲል ጽፏል።
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የሕዳሴ ግንባታን ከጀመረችበት ጊዜ እስከ ተጠናቀቀበት ቅርቅ ጊዜ ድረስ ከሱዳን እና ግብፅ ጋር አለመግባበት ውስጥ ቆይታለች። በተለይም በግብፅ በኩል ጠንከር ያለ ጫና የመፍጠር ጥረት በተለያዬ አቅጣጫ አሁንም ድረስ እያስተናገደች ነው።
ላለፉት አስራ አራት ዓመታት በአባይ ወንዝ ጉዳይ ላይ ከስምምነት ለመድረስ የሦስትዮሽ ድርድር ሲካሄድ የነበረ ቢሆንም፣ እስካሁን ሁሉን አቀፍ መግባባት ላይ መድረስ አልተቻለም።
ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የምታነሳው የአባይን ወንዝ በፍትሐዊነት የመጠቀም አቋም አልቀየረችም። የግድቡ መገንባት በግብፅም ይሁን በሱዳን ላይ እንደሚባለው የውሃ እጥረት እንደማያስከትል፣ በሙሌት ሂደቱም ይሁን ከተጠናቀቀም በኋላ በተግባር ታይቷል።
ይሁን እንጂ የግብፅ የቅኝ ግዛት እሳቤ የተጠናወተው ጫና የመፍጠር አባዜ፣ በአሜሪካ በኩል እጅ ለማስጠምዘዝ ፍላጎት እንደቀጠለ ነው። የትራምፕ በግልፅ ግለሰባዊወገንተኝነት የተጫነው የአደራዳሪነት ፍላጎትም፣ በገንዘብ ጭምር የሚገዛው ከካይሮ የእጅ አዙር ጨና ጋር ሚገናኝ ነው።
የኢትዮጵያን
እጅ ለመጠምዘዝ በመጀመሪያ የትራምፕ ሥልጣን ጊዜ ድርድር፣ ከግብፅ ገንዘብ የተቀበሉ ሴናተር ጠፋተኛ መባላቸው ይታዘሳል። የአሜሪካን
ሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ይመሩ የነበሩት የኒው ጀርዚ ሴናተር ቦብ ሜኔንዴዝ፣ በአባይ ጉዳይ ለግብፅ ጥቅም ለመሥራት ጉቦ መቀበላቸው
ተረጋግጦ ከወራት በፊት የ11 ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል፡፡
ምንም
እንኳን ትራም በመጀመሪያ የሥልጣን ጊዜያወቸው እጅ ለመጠምዘዝ ሙከራ ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም፡፡ አሁንም ቢሆን ለግብጽ ውግንና
ይዘው ውዝግቡን እንፈታዋለን ማለታቸው የተለየ ለውጥ ያመጣል ተብሎ አይጠበቅም፡፡
.png)
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ