ኢትዮጵያን ማን ያሻግራት?

 ኢትዮጵያን ማን ያሻግራት? 

በጋዜጠኛ መርሻ ጥሩነህ

በግራ በቀኝ ወጀብ በበዛበት ሁኔታ ቀናት ወራትን፣ ወራት ዓመታትን እየወለዱ ጊዜ እየነጎደ ነው፡፡ 

ዓመቱ እጅግ ፈታኝ ዓመት ሆኖ ብቻ አላለፈም፣ ይልቁንም ለተተኪው ዓመት አዳሪ ችግሮችን አሸግሯል፡፡ በዚህ መሰል ወጀብ ውስጥ እያለፈች የምትገውን ኢትዮጵያ አሸጋሪ ትሻለች፡፡

ኢትዮጵያ ፈታኝ ወቅት ላይ እንደምትገኝ አሁን ላይ የገጠሟች ዘርፈ ብዙ ችግሮች ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ መሆኑን፣ ከኃይማኖት ተቋማት እስከ፣ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ ፖለቲካ አዋቂዎች፣ ከማኅበረሰብ አንቂ እስከ ተርታው ማኅበረሰብ በየፊናቸው ያረጋገጡት ሀቅ ነው፡፡

ጥያቄው ኢትዮጵያን ማን ያሸግራት? የሚለው ነው፡፡ በተከታወዩ ጽሑፍ የ2015 አብይት ጉዳዮች ምን እንደነበሩና ኢትዮጵያን ማን ያሻግራት የሚሉትን ጉዳዮችን በወፍ በረር እንመለከታለን፡፡

የ2015 አበይት ጉዳዮች ምን ነበሩ?


የተጠናቀቀው 2015 እንዴ አገር ለኢትዮጵያ፣ እንዴ ዜጋ ለኢትዮጵያን በብዙ ችግሮች ታጅቦ ያለፈ ዓመት እንደነበር፣ በዓመቱ የተከናወኑ የፖለቲካ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አበይት ጉዳዮች አመለካች ናቸው፡፡


ü  የሰሜኑ ጦርነት ማብቃት

የሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ምምነት መሰረት ከሁለት ዓመት ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ ያበቃው፣ በተሸኘው 2015 ሁለተኛ ወር ላይ ነበር፡፡ ጥቅምት 23/2015 የፌዴራል መንግሥት እና ህወሓት በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ጦርነቱን ለማቆም የተስማሙበት ዓመት ሆኖ አልፏል፡፡

ይሁን እንጂ በሰላም ስምምነቱ መሰረት ይፈጸማሉ በተባሉ ጉዳዮች ላይ አሁንም ውዝግበቶ መነሳታቸውን ቀጥለዋል፡፡ የሚነሱት ውዝግቦች በአማራ እና ትግራይ ክልሎች መካከል የተፈጠረው ወልቃይት፣ ራያና ጠለምት የይገባኛል ጥያቄ እና የኤርትራ ሰራዊት ከኢትዮጵያ ደንበር አለመውጣት ናቸው፡፡

እነዚህ ሁለት ዋና ዋና ሁነቶች ከፍተኛ ስጋት የፈጠሩ ሲሆን፣ የፌዴራል መንግሥቱ ሁለቱንም ጉዳዮች እንዳጽፈጽም በሕወሓት በኩል ከፍተኛ ውትወታ እየቀረበበት ነው፡፡

በአንጻሩ በአማራ በኩል የይተባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎች ከጦርነቱ በኋላ ወደ አማራ ክልል ተካለዋል አሳልፈን አንሰጥ የሚል አቋም ተፈጥሯል፡፡ የኤርትራ ሰራዊት ወደ ድንበሩ የመመለስ ጉዳይ የፌዴራል መንግሥቱ ሚና ቢሆንም እስካሁን አልመፈጸሙ ግጭት እንዳይፈጥር ስጋት እንደፈጠረ ነው፡፡

ü  የክልል ልዩ ኃይል አደረጃጀት መፍረስ

በዚሁ ዓመት ከተከናወኑ አበይት ጉዳዮ መካከል የፌዴራል መንግሥት የክልል ልዩ ኃይል አደረጃጀቶችን በይፋ ያፈረሰበት ውሳኔ አንዱ ነው፡፡ ለክልል ልዩ ኃይሎች መፍረስ ምክንያት ሆኖ የቀረበው ኢ-ሕገ መንግሥታዊ፣ የክልል መንግሥታት የፌዴራል መንግሥቱን ኃይል የሚገዳደር ወታደራዊ ኃይል መገንባታቸውና አንዳቸው ከአንዳቸው ጡንቻ የሚለካኩበት ሁኔታ ስጋት መፍጠሩ ነው፡፡

በክልል ልዩ ኃይል አደረጃጀት ላይ የሕጋዊነት ጥያቄን ተንተርሶ የገባውን ስጋት ለማስቀረ፣ ልዩ ኃይሎችን አፍርሶ ወደ መከላከያ፣ ፌዴራል ፖሊስና ወደ ክልል መደበኛ የጸጥታ ኃይል እንዲቀላቀሉ አድርጓል፡፡

የክልል ልዩ ኃይል አደረጃጀት ላይ ከክልል መነግሥታት እስከ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ስምምነት ቢኖርም አፈጻጻሙ ላይ ሰፊ ልዩነት ተፈጥሯል፡፡ በዚህም አተገባበሩ ላይ ጥያቄዎች ተነስቶ በተለይ በአማራ ክልል ውሳኔው ክልሉ ቀድሞውንም በነበረበት ውጥረት ላይ ተደርቦ ሌላ ችግር አስከትሏል፡፡

ü  የአማራ ክልሉ ውጊያ መቀስቀስ

ከአስከፊው የሰሜኑ ጦርነት ማብቃት በኋላ ኢትዮጵያን ወደ ሌላ የእርስ በእርስ ጦርነት ያስገባ ግጭት በአማራ ክልል የተከሰተው በዚሁ ዓመት አጋማሽ አካባቢ ወዲህ ነው፡፡ በክልሉ በስፋት በሚንቀሳቀሰው ፋኖ እና መከላከያ መካከል አልፎ አልፎ ይታይ የነበረው ግጭት ከአንድ ወር በፊት ወደለየለት ውጊያ መግባቱ የዚህ ዓመት ጉልህ ክስተት ሆኗል፡፡

የሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ውጊያ አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን፣ አገሪቱ ከጦርነት ወጣች ስትባል ሌላ ጦርነት ውስጥ የገባችበትን ሁኔታ መፍጠሩ ብዙዎችን አሳዝኗል፡፡ ችግሩ ገና በውጥረት ደረጃ ላይ እያለም ይሁን ከፈነዳ በኃላ የተለያዩ ዓለም አቀፍ እና አገር አቀፍ አካላት፣ ኃያላን አገራት፣ የኃይማኖት ተቋማትና ሌሎችንም በሰላም እንዲፈታ ቢጠይቁም ሳይሳካ ዓመቱ ተሸኝቷል፡፡

እስካሁን በተደረጉ ውጊዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች በመከላከያ የድሮንና ከባድ መሳሪያ  ጥቃት፣ እንዲሁም በሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ተባራራ ተተኳሾች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡

ü  የኦነግ ሸኔ እና መንግሥት ድርድር መክሸፍ

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ የገባው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር(ኦነግ) ወታደራዊ ክንፍ የነበረው ኃይል፣ ከመንግሥት ጋር አለመስማማቱን ተከትሎ ከኦነግ ተገንጥሎ ወደ ትጥቅ ትግል ከገባ በኋላ የተጀመረው ድርድር የከሸፈው በዚሁ ዓመት ነው፡፡

ለዓመታት የዘለቀቀው መንግሥት “ኦነግ ሸኔ” ሲል በአሸባሪነት የፈረጀውና ራሱን “የአሮሞ ነጻነት ሰራዊት” ብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን እና የመንግሥትን ውጊያ ይቋጫል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት ነበር፡፡

ይሁን እንጅ በምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር ታንዛኒያ ላይ የተካሄደው ድርድር ያለ ውጤት መቋጨቱን ተከትሎ፣ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎችና የታጣቂ ቡድኑ ውጊያ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ በዚሁ ምክንያት በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሰላማዊ ሰዎች ግድያና የክልሉ ህዝብ ቁስቁልን እንደቀጠለ ነው፡፡

ü  የሸገር ከተማ ምስረታና የዜጎች መፈናቀል

አወዛጋቢ የሆነውን አዲስ አበባ እና ኦሮሚያ ክልል ወሰን እልባት ይሰጣል ተብሎ በዚሁ ዓመት የተከናወነው የወሰን ማከለልን ተከትሎ፣ የሸገር ከተማ አስተዳደር የተወለደው በዚሁ ዓመት ነበር፡፡

ኦሮሚያ ክልል የመሰረተው አዲሱ ከተማ አስተዳደር ከተመሰረተ በኋላ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የሚኖሩባቸው ቤቶችና የሚገለገሉባቸው ቤተ እምነቶች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ፈርሰዋል፡፡ መንግሥት የቤት ፈረሳውን ያከናወነው ከከተማ አስተዳደሩ አጠቃላይ ይዞት ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው በሕገ ወጥ መንገድ የተገነባ ነው በማለት ነው፡፡

የቤት ፈረሳው ተግባሩ የዜጎችን መጠላያ የማግኘት ሰብዓዊ መብት የላከበረና ምንም አይነት ቅድመ ሁኔታና አማራጭ ያላስቀመጠ መሆኑን፣ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ሁኔታ ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ የዜጎች ህይወት ቀውስ ፈጥሯል፡፡ የቤት ፈረሳው ሰለባ የሆኑ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ጊዜያዊ የመጠለያ ካምፕ እንኳን ባለመግኘታቸው በየቦታቸው ሜዳ ላይ ወድቀው የሕግ ያለህ፣ መንግሥት የለም ወይ፣ ዜጋ አይደለንም ወይ የሚሉ ጩኸቶችን እያሰሙ እስካሁን አሉ፡፡

የመንግሥት ውሳኔ ዜጎችን በተለይ ለኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ በከፍተኛ ሁኔታ ያጋለጠ መሆኑን ተከትሎ፣ ከሰብዓዊ መብት ተቋማት እስከ ሃይማኖት ተቋማት ዜጎችን መጠለያ የማግኘት መብታቸው እንዲከበር ቢጠይቁም ሰሚ ሳይገኝ፣ ዜጎችንም የሰቆቃ ህይት መግፋታቸውን እንደቀጠሉ ዓመት አልፏል፡፡

ü  የአዳዲስ ክልሎች ውልዴት

የኢትዮጵያ መንግሥታዊ አወቃቀር የብሔር ፌዴራሊዝም ላይ የተመሰረተ መሆኑን ተከትሎ፣ በተለይ የኢትዮጵያ ተምሳሌት ተደርጎ የሚሳለው ከደቡብ ኢትዮጵያ በኩል በርካታ የክልልነት ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡

የተነሱት የክልልነት ጥያቄዎች መሰረት አደርጎ በዚሁ ዓመት መጨረሻ ወራት ላይ የቀድሞው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ለሁለት ተከፍሏል፡፡ በዚህም “ማዕከላዊ ደቡብ ኢትዮጵያ” እና “ደቡብ ኢትዮጵያ” የተሰኙ ሁለት ክልሎች አዲስ ክልሎች ተወልደዋል፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ የተነሱት የክልልነት ጥያቄዎች ከ10 በላይ ሲሆኑ፣ የቀድሞው ክልል አሁን ላይ ወደ አራት ክልል ተከፍሏል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም እንዴ ጉራጌ፣ ጋሞ፣ ከምበታ ጠንባሮና ወላይታ የመሳሰሉ ዞኖች የክልልነት ጥያቄያቸውን ማቀንቀናቸውን ቀጥለዋል፡፡

የክልልነት ጥያቄያቸውን ጠንከር አድርገው በምክር ቤታቸው ጭምር ያነሱ እንደ ጉራጌ ባሉ ዞኖች በተከታታይ ተቋውሞዎች፣ አድማዎችና ሰላማዊ ሰልፎች ተደርገዋል፡፡ በተቃውሞ እንቅስቃሴው ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች መኖራቸውና ለእስር የተዳረጉ ወጣቶች እንዳሉ የሚታወስ ነው፡፡  

ü  የቤተ እምነቶች ፈተና

2015 በቤተ እምነት ተቋማት ዘንድ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ፣ በተለይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዘንድ የመካፈፈል አደጋ የተደቀነበት ዓመት ነበር፡፡

ቤተ ክርስቲያኗ የገጠማት የመከፋፈል አደጋ ከኦሮሚያ እና ትግራይ ክልል አባቶች የተነሳ ሲሆን፣ በሁለቱ ክልሎች ሲኖዶስ እንመሰርታለን ማለታቸውን ተከትሎ የተነሳ ነበር፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት የተነሳው የኦሮሚያ ሲኖዶስ ምስረታ ጉዳይ በዚሁ ዓመት ግሃድ ወጥቶ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የሆኑ ሦስት ጳጳሳት፣ የኦሮሚያና ብሔር ብሔረሰቦች ሶኖዶስን መስርተናል ብለው ሊቃና ጳጳሳት መሾማቸው ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሯል፡፡

በዚሁ ምክንያት ከፍተኛ ተቃውሞና ቁጣ ተቀስቅሶ በርከታች ሕይወታቸውን ሲያሰጡ በመቶዎች የሚቆተሩ ሰዎች ለእስር ተዳርገዋል፡፡ ችግሩ ከፍተኛ አደጋ መደቀኑን ተከትሎ መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ውጥረቱን ለማድረግ ጥረት ካደረገ በኋላም፣ የጉዳዩ ጠንሳሾች በተግበራቸውን ቀጥው ችግሩ እንዴገና አገርሽቶ እንቅስቃሴው አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡

ሌላኛው በዓመቱ ፈተና የገጠመው የሙስሊም ቤተ እምነት ሲሆን፣ በተለይ ከሸገር ከተማ አስተዳደር ምስታ ጋር በተያያዘ በርካታ መስጊዶች መፍረሳቸው በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ቁጫ የቀሰቀሰ ነበር፡፡

ከተማ አስተዳደሩ መስጊዶችን ማፍረሱን ተከትሎ ለተቃውሞ አደባባይ የወጣው የሙስሊም ማኅበረሰብ፣ ከሞት እስክ አካል ጉዳት፣ ከእስራት እስከ ግርፋት ችግሮችን አሳልፏል፡፡ ችግሩን ለመፍታት የእምነቱ አባቶች ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጋር ባደረጉት ውይይት ቤተ እምነቶቹ እንዴገና ይሰራሉ ተብሎ ችግሩ ረግቧል፡፡

ü  ረሃብና ዕርዛት

በዚሁ ዓመት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን በጦርነት፣ እርስ በእርስ ግጭት፣ በድርቅና በቤት ፈረሳ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉበት ሁኔታ በስፋት ተከስቷል፡፡ በተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ለረሃብና ዕርዛት ተጋልጠው በሺዎች የሚቆጠሩት ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡

ችግሩ አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን፣ በዚህ ወቅት እንኳን ከ4 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በችግር ላይ ይገኛሉ፡፡ ለተፈናቃዮችና እርዳታ ፈላጊዎች ውጭ ድርጅቶች የሚያቀርቡት ስንዴ መሰረቁን ተከትሎ፣ የተቋረጠው የውጭ ድጋፍ ረሃብ ፈጥሮ ይገኛል፡

ü  የዓባይ ግድብ አራተኛ ዙር የውሃ ሙሌት

ኢትዮጵያ ገና ከጅምሩ ዓለም አቀፍ ጫና ያስተናገደችበት የታለቁ ህዳሴ ግድብ አራታ ዙር የውሃ ሙሉት የተጠናቀቀው፣ በዚህ ዓመት የመጨረሻ ቀናት ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ምንም እንኳን ዜጎቿ በፖለቲካ የሚራኮቱ ቢሆንም፣ በዓባይ ጉዳይ የጎላ ልዩነት ሳያሳዩ እስካሁን ባለው ስኬት እየተደረሰቱ ድጋፋቸውን ቀጥለዋል፡፡

በጥቅል ዓመቱ ኢትዮጵያ ከአንድ ችግር ወደ ሌላ ችግር የተሸጋገረችበት፣ ከአንዱ ደም አፋሳሽ ጦርነት ማብቃት ማግስት ወደ ሌላ ደም አፋሳሽ ጦርነት የገባችበት ሆኖ አልፏል፡፡ የተቀበልነው አዲሱ 2016 ፈታኝ ከነበረው 2015 ዓመት የተዋረሳቸው ውስብስብ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አሉ፡፡

Ø  ኢትዮጵያን ማን ያሻግራት?

2015 እጅግ ፈታኝ ዓመት ሆኖ ብቻ አላለፈም፣ ይልቁንም ለተተኪው 2016 አዳሪ ችግሮችን አሸግሯል፡፡ በዚህ መሰል ወጀብ ውስጥ እያለፈች የምትገነውን ኢትዮጵያ አሸጋሪ ትሻለች፡፡

ኢትዮጵያ ፈታኝ ወቅት ላይ እንደምትገኝ አሁን ላይ የገጠሟች ዘርፈ ብዙ ችግሮች ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ መሆኑን፣ ከኃይማኖት ተቋማት እስከ፣ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ ፖለቲካ አዋቂዎች፣ ከማኅበረሰብ አንቂ እስከ ተርታው ማኅበረሰብ በየፊናቸው ያረጋገጡት ሀቅ ነው፡፡

ጥያቄው ኢትዮጵያን ማን ያሸግራት? የሚለው ነው፡፡

ኢትዮጵያ ዙሪያገባውን ከገጠማት ፈታኝ ችግር ለማውጣት ትልቁ ኃላፊነት በመንግሥት ተካሻ ላይ የሚወድቅ መሆኑን የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ መንግሥት እንዴ መንግሥት ችግሮችን በሆዴ ሰፊነት ለመፍታት የሚከፈል ዋጋም ካለ መክፈል እንደላበት የአዲስ ዓመት ሰላም ጥሪ ያቀረቡ አካላት በስፋት ገልጸዋል፡፡

በዋነኝነት ትለቁ የኢትዮጵያ አሁናዊ ችግር የሆነውን ቤአካባቢው የሚታየውን ውጊያ ማቆምና ልዩነቶችን በድርድር መፍታትና ሰላማዊ ሁኔታ መፍጠር ኢትዮጵያን ለማሸገር ሁነኛ መፍትሔ ነው፡፡

በሌላ በኩል ከመንግሥት ጋር እየተፋከለሙ የሚገኙ ኃይሎች ለንግግር ዝግጁ መሆን ኢትዮጵያን ሊያሸግር እንደመሚችል ይታመናል፡፡ ሐቀኛ ንግግርና ድርድር ለማካሄድ ከታጠቂዎችም ይሁን ከመንግሥት መተማመንና ቁርጠኝነት ያስፈልጋል፡፡

ተፋላሚ ወገኖችን ለማቀራረብና ልዩነታቸውን በንግግርና በድርድር እንዲፈቱ ለማድረግ የኃይማኖት ተቋማት፣ አገር ሽማግሌዎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ሚዲያዎችና ሌሎችም ባለድርሸሸ አካላ የየደርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡

በጠቅሉ ኢትዮጵያ በሁኑም ባለድርሻ አካላት ቅርጠኝነትና ሐቀኝነት የምትሻግር ናት እና ኢትዮጵያን ማሻገር የሚችሉት ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡ ያ ማለት ሁኑም በየደረጃው፣ በየደርሻውና በየፊናው አወንታዊ አብርከቶውን ሲወጣ ነው፡፡

 

አዲሱ 2016 ኢትዮጵያ ሰላሟ የሚመለሰበት፣ ዜጓቿ ከችግርና መከራ ወጥተው በሰላም፣ በፍቅርና በትብብር የሚኖሩበት እንዲሆን ምኞቴ ነው፡፡

መልካም አዲስ ዓመት!

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

የአብይ አህመድ እና ኢሳያስ አፈወርቂ መዋጊያዎች!

ዳግማዊ ትግራይ በአማራ ላይ!