ዳግማዊ ትግራይ በአማራ ላይ!

ዳግማዊ ትግራይ በአማራ ላይ!


በጋዜጠኛ መርሻ ጥሩነህ

ከሚሊዮን ዜጎች እልቂት እስከ ሚሊዮች አርዛት፣ ከሚሊዮኖች መፈናቀልና ጉስቁልና እስከ ትሪሊዮን ብር ውድመት ያስከተለው፣ የትግራይ እርስ በእርስ ጦርነት ዛሬም በሌላ ተረኛ ሕዝብ ላይ ተደቅኗል የሚሉ ድምጾ ከሰሞኑ ከየአቅጣጫው በስፋት ተሰምተዋል፡፡

የእነዚህ ድምጾች መነሻ ከትግራዩ ጦርነት ማብቃት ማግስት በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቀዎች እና በመንግሥት በካከል የተቀሰቀሰው ግጭት በሰላማዊ መንገድ ይፈታል ተብሎ ሲታሰብ ወደለየለት ውጊያ መሸጋገሩር ነው፡፡

በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ግጭት ከዚህ ደቀም ትግራይ ክልል የሆነውን የሚደግም አካሄዶችን በግልጽ እያሳየ ነው። የአማራ ክልሉ የጸጥታ ችግር በትግራይ ጦርነት ወቅት የተፈጸሙ ተፊ ጥቃቶችና ጥፋቶች ሊስከተል እንደሚችል፣ አደባባይ የወጡ ማስረጃዎች ከወዲሁ ፍንትው ብለው እየታዩ ነው፡፡

በትግራዩ ጦርነት ጅማሮ ላይ የታዩ ፍረጃዎች፣ የክልል መንግሥታት የጦርነት ድጋፍ ዘመቻ፣ የእነ ዳቆን ዳንኤል ክብረትና መሰሎቹ የተለመደ ጦርነት የማቀጣጠል ተግባር፣ በከተሞች ጭምር የሚፈጸሙ ድሮን ጥቃቶች፣ የሰላማዊ ሰዎች ግድያ፣ አማራ ተወላጆች ጅመላ እስር፣ በፌዴራል መንግሥቱ በኩል በግልጽ ተጀምሯል።

ያኔ በትግራዩ ጦርነት ዋዜማ ከመቀሌ አዲስ አበባ፣ ከአዲስ አበባ መቀሌ በብልጽግና እና በሕወሓት መካከል ሲዥጎደጎዱ የነበሩ የቃላት ጦርነቶችና እርስ በእርስ መፈራረጆች፣ ዛሬም በመንግሥት እና በአማራ ክልል በመንግሥት ላይ ባመጹ ኃይሎች መካከል በግልጽ ተጀምሯል፡፡

የዛሬን አያድርገው እና ያኔ በለውጡ ሰሞን ሕወሓት ከአዲስ አበባ ተነቅሎ፣ መቀሌ ሲመሽግ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድና መሰሎቻቸውን የፍረጃ ቃላት ተቀብለው በአደባባይ ሲያስተጋቡ የነበሩ የገዥው ብልጽግና ሰዎች ዛሬም በተመሳሳይ መንገድ ተከስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕወሓትን “ጁንታ” ብለው ከፈረጁት በኋላ በወቅቱ በውድም ይሁን በግድ ከመንግሥት ጎን የተሰለፈ ዘማችና አዝማች ቃሉን አንግሦስት ነበር፡፡ ከፖለቲካ ባለሥልጣናት እስከ ወታደራዊ አዛዥ፣ ከሰፈር ካድሬ እስከ ሚስኪን አርሶ አደር በወቅቱ የፍረጃ ዘመቻ የሰከረው ሁሉ ዛሬ ደግሞ በአዲስ ቃል ተከስቷል፡፡

የአማራ ክልሉ ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ ደግሞ የመንግሥት አጀንዳ ፈጣሪ የሆኑት እነ ዳንኤል ከብርት በትግራዩ ጦርነት አዝምተው ሲያሞካሹት የነበረውን ፋኖን “ጃውሳ” የሚል ፍረጃ ለጥፈውበት ከእንደከዚህ ቀደሙ የጦርነት ድለቃ ዘመቻ ላይ ተሰማርተዋል፡፡

“ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራ ነሽ ይሏታል” እንደሚባለው፣ በትግራዩ ጦርነት ወቅት ሁሉም ክልሎች ዘማች እንደሆኑት ሁሉ፣ ከመንግሥት ጋር አብሮ በዘመተው ፋኖ ታጣቂዎች ላይ ከጦርነት ማግሥት አደገኛ ፍረጃዎች አስቀድመው ተከፍተዋል፡፡

ፍረጃዎቹ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እስከ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ከከንቲባ አዳነች አቤቤ እስከ ብልጽግና ፕሮፖጋንድስቶች በአደባባይ የተነገሩ መሆናቸ አሁን ለተፈጠረው ችግር አቀጣጣይ ሆነዋል ማለት ይቻላል፡፡

የመጀመሪያዋ የአደባባይ ፍረጃ ፈር ቀዳጅ አዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሲሆኑ፣ ከንቲባዋ በዚሁ ዓመት በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ተቀስቅሶ የነበረው ግጭት አስመልኮ አስተያየት ሲሰጡ “ጽንፈኛው ፋኖ” ሲሉ ተደምጠው ነበር፡፡

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ፊለድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ደግሞ የክልል ልዩ ኃይሎችን መፍረስ ተከትሎ፣ የአገሪቱንና የክልሎችን የጸጥታ አለቆች ሰብስበው “ፋኖ አማራ ክልልን ፓራላይዝድ አድርጓል፣ ፋኖ የአማራ ልዩ ኃይልን ጨፍጭፏል” በማለት ትላንት ባወደሱት ፋኖ ላይ ተደራራቢ ፍረጃዎችን ጨነውበታል፡፡

ጠቅለይ ሚኒሰትሩም አስቀድመው በፓርላማው ፊት “ጥቁር ክላሽ ታጣቂ ብሎ ፋኖ የለም” ሲሉ፣ ከጦራቸው ጎን አሰልፈውት ሲያበቁ የመከላከያን ጥቁር ክላሽ ቀምቷል በማለት ሲከስቱ ነበር፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩም ይሁን የሌሎች ባለሥልጣናት ፍረጃና ክሶች መንግሥት ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር የገባበትን ልዩነት በንግግር እንዳይፈታ እንደ አንድ እንቅፋት መሆኑን የማይካድ ሃቅ ነው፡፡

በአሁኑ የአማራ ክልል ምስቅልቅል ዋዜማም ይሁን ከግጭቱ መቀስቀስ በኋላ የተለጠፉ ፍረጃዎች ሕወሓት ላይ ከተደረገው መንግሥታዊ ዘመቻ የተለየ አይደለም ማለት ይቻላል፡፡ በየቅጣጫው የሰላም አማራጮችን ቅድሚያ እንዲሰጣቸው የሚጠይቁ ጥሪዎች እየጎረፉ ባሉበት ሁኔታ፣  የተጀመረው ዘመቻ ነገሮችን ከማባበስና እልቂት ከመፍጠር የዘለለ ትርፍ እንደሌለ ቢታወቅም ችግሩ በመንግሥት ሰዎች ብሷል፡፡

በአማራ ክልል የተቀተቀሰው ውጊያ ከትግራዩ የሚለየው አንድ መሰረታዊ ልዩነት አለ፡፡ ይሄውም የትግራዩ ጦርነት ኢትዮጵያን 27 ዓመት በበላይነት ሲመራ በነበረና የክልል መንግሥትነት ሥልጣን በነበረው ሕወሓት እና በመንግሥት መካከል የተደረገ ነበር፡፡

የአማራ ክልሉ ደግሞ የክልሉ መንግሥት የሌለበት ግን ደግሞ ቀላል የማይባል የሕዝብ ድጋፍ ባለው፣ ነገር ግን መንግሥታዊ ስልጣንም ከሌለው እንደ ሕወሓት የአገሪቱን የጦር መሳሪያ ያልታጠቀው ፋኖ ጋር መሆኑ ነው፡፡

በአጭሩ የትግራዩ ጦርነት በክልል መንግሥት እና በፌዴራል መንግሥት መካከል የተደረገ ሲሆን፣ አማራው ደግሞ የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት ጎን ከመሰለፍ አልፎ ክልሉን የማስተዳደረ ሥልጣንኑን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳልፎ መስጠቱ ነው፡፡

በክልሉ በታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት ክልሉን እንዲመራ የተዋቀረው ወታደራዊ አስቸኳይ ጊዜ ዕዝ መምሪያ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ ይህ ማለት ክልሉን የሚመራው ወታደራዊ አስተዳደር ታዛዥነት ከዕዙ መሪ አቶ ተመስገን ጥሩነት ቀጥሎ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የበላይነት የሚመራ ነው፡፡

በትግራይ ክልል ሕወሓት አና የፌዴራል መንግሥት ጦርነት እንደገጠሙ የተወሰደው የመጀሪያው እርምጃ፣ በተመሳሳይ በአማራ ክልሉ የመከላከያ እና የፋኖ ታጣቂዎች ይፋዊ ውጊ ማግስት ተድሟል፡፡ የመጀመሪያው እርምጃ አስቸኳይ ጊዜ አውጆ ክልሉን በወታደራዊ ኃይል መቆጣጠርና የኃይል እርጃ መውሰድ ነው፡፡

የፌዴራል መንግሥት ክልሎችን መቆጣጠር ወይም ጣልቃ መግባት የሚችለው ልክ አሁን እንዳደረገው ጥያቄ ሲቀርብለት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት በሚያቋውመው ወታደራዊ አስተዳደር ነው፡፡

እዚህ ጋር የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደ/ር ይልቃል ከፋለ፣ ክልሉን ለፌዴራል መንግሥት አሳልው የሰጡበት ውሳኔ የክልሉ ምክር ቤት የማያውቀውና ሕጋዊ መሰረት የሌለው ነው መባሉን ማስታወስ ይገባል፡፡

አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀ ማግሥት በትግራይ ጦርነት እንደነበረው የክልል መንግሥታት ከፌዴራል መንግሥት ጎን ቆመው ወደ አማራ ክልል ለመዝመት ያላቸውን ዝግጁን አረጋግጠዋል፡፡

እንደ አለመታደል ሆኖ ጦርነቱ በየተራ እየዞረ ቢሆንም፣ የክልል መንግሥታት የፌዴራል መንግሥቱ ያወጀውን ሁሌ ተቀብለው ያለ ምንም ማቅማት ውረድ እንውረድ ዘመቻውን ያጣጡፉታል፡፡

ትላንት  በግድ በልጽግ ተብሎ አልበጽግም ባለው ሕወሓት ሰበብ በትግራይ ክልል በተካሄውን የእርስ በእርስ ጦርነት፣ ከሰንጋ እስከ ወታደር፣ ከጦርነት ድጋፍ ሰልፍ እስከ ቢሊዮን ብሮችን እስከማዋጣት ግንባር ቀደም የነበሩ ክልሎች ዛሬም በአማራ ላይ እንዘምታለን እያሉ ነው፡፡

ልክ እንደ ሕወሓትና ብልጽግና ከትግራዩ የእርስ በእርስ ጦርነት መማር የነበረባቸው የመንግሥት ፖለቲከኞችም ይሁኑ፣ በፋኖ በኩል የተሰለፉ ደጋፊዎችና ፖለቲከኞች በየፊናቸው ውረድ እንውረድ መባባላቸውን ቀጥለዋል፡፡

በዚህ ውረድ እንውረድ ውስጥ በክልሉ ትልልቅ ከተሞች በተለይ ባህር ዳር ከተማ ላይ በርከታ ሰላማዊ ሰዎች በግፍ ተገድለዋል፡፡ እንደ ጎንደር፣ ደብረ ብራሃን፣ ደብረ ማርቆስና ሌሎች ከተሞች ላይ የተቀሰቀሰው ውጊያ ጋብ ካለ በኋላ፣ መንግሥት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የድሮን ጥቃት መፈጸም ጀምሯል፡፡

የድሮን ጥቃት የታጠቁ ሰዎችን ብቻ እንደማያጠቃ በትግራዩ ጦርነት የታየ ሃቅ ሲሆን፣ በአማራ ክልሉም ገና ከጅምሩ በተፈጸመው የድሮን ጥቃት በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የሚያረጋግጡ መረጃዎች ወጥተዋል፡፡

መንግሥት ደብረ ብርሃን፣ ፍኖተ ሰላምና ብሬ ላይ በፈጸመው የድሮን ጥቃት በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የሰብዓዊ መብት ጠቋማትና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በስፋት ዘግበውታል፡፡

በክልሉ ውጊያ ከተጀመረ በኋላ ስላለው ሁኔታ ሪፖርት ያወጣው ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፣ በደብረ ብርሃን፣ ፍኖተ ሰላም እና ቡሬ ከተሞች ሰላማዊ ሰዎች እና በመኖሪያ ሕንጻዎች ላይ ጉዳት ያደረሱ የአየር ጥቃቶች ስለመፈጸማቸው ተዓማኒነት ያላቸው ሪፖርቶች ደርሰውኛል ብሏል።

በባሕር ከተማ በበርካታ ሰላማዊ ሰዎች በመንገዶች እና በመኖሪያ ቤታቸው መገደላቸውን ያረጋገጠው ኮሚሽኑ፣ በሸዋ ሮቢት ደግሞ በመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጭ የሆነ ግድያ መፈጸማቸውን አስታውቋል፡፡

በትግራይ ክልል ጦርነት የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎ ፈጽመዋቸዋል የተባሉ ደርጊቶች በአማራ ክልሉ ውጊያ መፈጸማቸው በስፋት እየተነገረ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ሸዋ ሪቢት ላይ የጸጥታ ኃይሎች ፈጽማጻል የተባለው ግድያ እውነት መሆኑን፣ የሟች ቤተሰቦች  አረጋግጠዋል፡፡

በከተማዋ አቅራቢያ ወደሚገኝ ወንዝ ተወስደው የተረሸኑ ዘጠኝት ወጣቶች ሲሆኑ፣ ወጣቶቹ ሰላማዊ ሰዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡ መሰል ጥቃቶች የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ባርዳር ከተማን ሙሉ በሙሉ ከተቆጣጠሩ በኋላ በስፋት መፈማቸውን ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸው ሰዎችን ጠቅሰው ለዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እዘገቡ ነው፡፡

በአዲስ አበባ፣ በቅርቡ በተዋቀረው ሸገር ከተማ አስተዳደር፣ ወልቂጤ እና ቢሾፍቱ ከተሞች የአማራ ብሔር ተወላጅ የሆኑ ሰላማዊ ሰዎች በስፋት መታሰራቸውን በስፋት እየተገለጸ ነው፡፡ ኢሰመኮ የህንኑ ማንነት ተኮር እስር በመፈጸም ላይ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

በትግራዩ ጦርነት ወቅት  አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆ  በዘመቻ መልክ ሲታሰሩ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒትሩ ጭምር ጉዳዩ ካለፈ በኋላ ያረጋገጡት ሀቅ ነበር፡፡ 

ሌላኛው በትግራይ ክልል ጦርነት ላይ የነበረው አሁን በአማራ ክልሉ እየተደገመ ያለ ዘመቻ፣ ባለሀብቶችን ማሸማቀቅ አንዱ ነው፡፡ በአማራ ባለሃብቶች ላይ ከወራት በፊት የተጀመረው አካውንት ከማገድ፣ ከአገር እንዳይወጡ እስከማገደብ የደረሱ ገደቦች መጠላቸው ተስመቷል፡፡

በትግራዩ ጦርነት መጀመር ዋዜማም ይሁን ከተጀመረ በኋላ የትግራይ ተወላጅ ባለሀብቶች የተለያዩ ጫናዎችን ሲደርሱባቸው ነበር፡፡ በመድናችን አዲስ አበባ የሚገኙ ባለቤትነታቸው የትግራይ ተወላጆች የሆኑ ኢንተርናሽናል ሆቴሎችን ጭምር የመዝጋት ዘመቻ መከናወኑ የሚታወስ ነው፡፡

በትግራይ ክልል እነዚያ ሁሉ ጥፋቶችና ጥቃቶች የተፈጸሙት መንግሥት “ሕግ ማስከበር” ብሎ በሰየመው እርምጃ የነበረ ሲሆን፣  አሁንም በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ውጊያ ተመሳሳይ ስያሜ ተስጥቶታል፡፡

ነገሩን ጠቅለል አድረገን ስንመለከተው፣ ከፍረጃ እስከ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ ከክልሎች የጦርነት ድጋፍ ድለቃና ዘመቻ እስከ ሕግ ማስከበር እርምጃ፣ ከተሞች ላይ በከባድ መሳሪያ ከተፈጸመው ድግያ እስከ ድሮን ጥቃት፣ ከኢንተርኔር መዘጋት እስከ ብር መከልከል የደረሱ ተመሳሳይ አካሄድ እየታዩበት ነው፡፡

ምንም እንኳን የትግራዩ ጦርነት እና አሁን በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ውጊያ መነሻ ልዩነት ቢኖረም፣ መንግሥት ተመሳሳይ እረምጃዎችን መውሰዱ ተመሳሳይ ጥፋት ማስከተሉ የማይቀር መሆኑ በግለጽ እየታየ ነው፡፡ 

በአማራ ክልል የተቀሰተው ቀውስ ዘርፈ ብዙ ገፊ ምክንያት እንዳሉት ከመንግሥት ባለሥልጣናት እስከ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቶዎችና ፖለቲከኞች የተቀበሉት ሀቅ ነው ማለት የሚቻልበት ሁኔታ አለ፡፡

ምንም እንኳን ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ መመለስ ያለባቸው ቢሆንም፣ በአማራ ክልል የተቀቀሰው የኃይል እርምጃ የታከለበት ሁኔታ፣ የተፈጠረው አማራ ሲያቀርባቸው የነበሩ ጥያቄዎች ምላሽ አለማግኘታቸውን ተከትሎ እንደሆነ በስፋት እየተገለጸ ነው፡፡

የክልሉን ሕዝብ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ የወከሉት ደመቀ መኮንን፣ ግጭቱ ከተከሰተ ማግሥት በሰጡት አስተያየት፣ የአማራ ሕዝብ ያልተመለሱ ጥያቄዎች እንዳሉት አረጋግጠዋል፡፡“ከለውጡ ብዙ የጠበቅናቸው ግን ደግሞ ምላሽ ያላገኘንባቸው ያላረኩንና ሌሎች ችግሮችና ስሜቶች ይኖራሉ፡፡” ሲሉ ለተፈጠረው ችግር ምላሽ ያላገኙ ጥያቄዎች መነሻ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በአማራ ክልል የታወጀውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማጽደቅ በተሰበሰበው ፓርላማ ፊት፣ የተቃውሞ ንግግር ያሰሙት የቀድሞው የክልሉ መሪ አቶ ገዱ አንድ አርጋቸው፣ የብልጽግና እና የአማራ ክልል ሕዝብ ግንኙነት ላይጠገን ተበጥሷል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ አቶ ገዱ “የአማራ ሕዝብ እንቅስቃሴ የተጠራቀመ ግፍና በደል የወለደው ቁጣ ነው፤ የተቆጣን ሕዝብ በኃይል ማሸነፍ አይቻልም” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ የሚታዩ አካሄዶች ልክ በትግራይ ክልል እንደነበረው “በሕግ ማስከበር ዘመቻ” ወደለየለት ጦርነት ሊያመሩ የሚችሉ ዘመቻዎች ተባብሰው ከቀጠሉ፣ በክልሉም ይሁን በአገር ደረጃ ሊያጋጥም የሚችለው ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ከባድ ሊሆን እንደሚችል የሚጠበቅ ነው፡፡

ይህ ማለት ግን አማራ ክልል ላይ ዳግማዊ ትግራይን ከመድገም ሊያተርፍ የሚችል አማራጭ የለም ማለት አይደለም፡፡ ዛሬም እንደ ትላንቱ እርስ በእርስ ተፈራርጆ እርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ከመግባት፣ በተለይ በመንግሥት በኩል ለንግግር ከልብ የመነጨ ፈቃደንኝት ካሉ ችግሩን አሁን ባለበት ሁኔታ ማስቆም የሚቻልበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡

ለዚህም ከኃይማኖት ተቋማት እስከ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ  ብዙዎች ከትናት እንማር እያሉ ከፍተኛ የሰላም ተማጽኖ እያቀረቡ ነው፡፡ ግጭቱ ገና ከመጀመሩ ሁሉም በሚባል ሁኔታ የኃይማኖት ተቋማት የሰላም ጥሪያቸውን ለተፋላሚ ወገኖች አቅርበዋል፡፡

አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት፣ እንደ አሜሪካ ያሉ ኃያላን አገራት፣ የአውሮፓ ሕብርት አባል አገራትና ሌሎችም መንግሥትም ይሁን የፋኖ ታጣቂዎች ግጭት አቁመው ለንግግር እንዲቀመጡ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ገና ከጅመሩ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች በስፋት መገደላቸውንና ከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ መሆኑን ያረጋገጠው ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ከሚሽንም፣ በአማራ ክልል፣ ተፋላሚ ወገኖች የሚያደርጉትን ግጭት ያለአንዳች ቅድመ ኹኔታ በአስቸኳይ እንዲያቆሙ እና ለውይይት እና ለሰላማዊ መፍትሔም ኹኔታዎች እንዲያመቻቹ ጥሪ አሳስቧል፡፡

አሁን የሚታየው ግጭት ወደ ለየለት ጦርነት ደረጃ አድጎ ለተራዘመ ጊዜ ቢቆይና ልክ እንደ ትላንቱ ዘርፈ ብዙ ኪሳራ ቢደርስ መደምደሚያው አንድ ነው፡፡

ለዚህ ማሳየ ሩቅ መሄድ ሳያስፈልግ፣ ሁለት ዓመት ሙሉ የት ቀረሽ ተባብለው ሲሰዳደቡና የአገር ሀብት የሆውን ወታደርና ድሃ ልጅ ያስጨረሱትን ብልጽግናና ሕወሓት መጨረሻ ማየት በቂ ነው፡፡

የብልጽግና እና የሕወሓት ባለሥልጣናት በሰው ልጅ ጭንቅላት ሊመነጭ የሚችል መሰዳደብና ጭካኔ የተሞላበት የጦርነት ጥቃት ውስጥ አልፈዋል፡፡ ባለሥልጣናቱና የጦርነቱ ጠንሳሾች ያን ሁሉ ነገር ከምንም ሳይቆጥሩት፣ የሕዝብ እልቂትና መከራ እንደዋዛ ተዘንግቶ አርስ በእርስ ተሸላልመው እየተሞጋገሱ ነው፡፡

አንድ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ስለ ሰሞነኛው አማራ ክልል ችግር ያጋሩትን ቀልብ የሚገዛ ሀሳብ አጋርቻችሁ ላብቃ፡፡

የሰብዓዊ መብት ተሟጎቹ ያሬድ ኃይለ ማሪያም “ሁለት አመት የቆየውን ጦርነት ለማስቆም የተፈረመው የሰላም ስምምነት ሰነድ ቀለሙ ሳይደርቅ፣ በአማራ ክልል ወደ ሌላ ዙር ደም አፋሳሽ ግጭት መግባታችን እጅግ ያሳዝናል፣ ያሳስባልም። እንደ ሕዝብም፣ እንደ መንግሥትም ትላንት ከገጠሙን መከራዎች እና ስህተቶቻችን መማር ያለመቻላችን ከግጭት አዙሪት እንዳንወጣ አድርጎናል የሚሉ ሀሳቦች በስፋት እየተሰሙ ነው።

መንግሥት ለአገር ውስጥ የፖለቲካ ግጭቶችና አለመግባባቶች ኃይልን ብቻ እንደ አማራጭ መጠቀሙን ካላቆመና  የፖለቲካ ኃይሎችም ሆኑ የክልል ታጣቂዎች ለሰላም ውይይቶች እድል የማይሰጡ ከሆነ ተያይዘን መጥፋታችን ነው። ከጦርነት በኋላ ብዙ ጉዳቶችን አስተናግዶ ሰላምን ፍለጋ ከመዳከር ይልቅ በሰላሙ ጊዜ ለዘላቂ ሰላም መስራት አገሪቱን ሊያረጋጋት ይችል ነበር።

እየሆነ ያለው ግን በተቃራኒው ነው። መንግሥት በዋነኛነት የግጭት አፈታት መንገዱን ሊፈትሽ ይገባል። የመንግሥት ባለሥልጣናት ከእልህ ወጥተው ስክነት ወደተሞላው ፖለቲካ መግባት ካልቻሉ ግን አገሪቱ ወደ ከፋ ሰብአዊ ቀውስና ከፍተኛ እልቂትን የሚያስከትሉ ግጭቶች ውስጥ ትገባለች፡፡” ሲሉ ሁኔታውን ገልጸውታል፡፡

ሰላም ለኢትዮጵያ!

 

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

የአብይ አህመድ እና ኢሳያስ አፈወርቂ መዋጊያዎች!

ኢትዮጵያን ማን ያሻግራት?