የአብይ አህመድ እና ኢሳያስ አፈወርቂ መዋጊያዎች!

  • ፋኖ፣ ኦነግ ሸኔና ብርጌድ ንሓመዶም ምንና ምን ናቸው?
ዕለቱ መጋቢት 24 /2010 ዓ.ም ነው፡፡ ወቅቱም ኢትዮጵያ በአራቱም አቅጣጫ በፖለቲካ ውጥንቅጥ የተወጠረችበት፡፡ በዚህ ውጥረት “ከሰማይ የወረደው ሙሴ” የተባለላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መሪ ሆነው ብቅ አሉ፡፡

ዕለቱ ኢትዮጵያዊነት፣ ሰላምና ፍቅር አየር ተሞላ፡፡ ኢትዮጵያዊያንም በፌስታ ፈነደቁና ተሰፋም አደረጉ፡፡ እነ ኦነግና ግንቦት ሰባትን ያቀፈችውን ኤርትራም የሰላም ጥሪ ቀረበላት፣ ተቀበለችም፣ ታጣቂዎቹም አገር አማን ብለው ወደ አገራቸው ገቡ፡፡

እነሆ እንዲህ አንዲህ እያሉ ወራት ዓመታትንን እየወለዱ፣ የኢትዮጵያዊነት ሸንገላ ቃላቶች በአየር ላይ እየከሰሙ፣ የተወጠረው  የፍቅር ፌሽታ በአቅጣጫው እየኮሰመነ፣ ታጣቂዎችም ተከዳን ብለው ጦራቸውን ወደ መንግሥት ካዞሩ ሰነባበቱ፡፡

በጣት ቀለበት የታሰረው የኢሳያስና የአብይም ወዳጅነት እነሆ እንዳልነበረ ሆኖ ጦር መማዘዝ ብቻ ቆርቷቸዋል፡፡ ሁለቱ መሪዎች በአንድ መድረክ ላይ ቆመው ማንም አይለየንም እንዳላሉ፣ በጎሪጥ መተያየት ጀምረዋል፡፡

ነገሮች እንዳልነበር ሆነው ተከረባብተው ጠላት ያሉትን ኃይል ለመውጋት በጋራ የተሰለፉ አካላት በየፊናቸው ጎራቸውን ለይተው አዲስ ጥምረት ለመመስረት እየጠሯሯጡ ነው፡፡ አብይና ኢሳያስ ሲለያዩ በታጠቁ ኃይሎች በኩል ለመወጋጋት ጉድጓድ እየማሱ ነው የሚለው ወሬ አየሩን ሞልቶት ሰንብቷል፡፡

ነገሩ በወሬ ብቻ የሚቆም አለመሆኑን ከሁለቱም አገራት በኩል ምልክቶች ታይተዋል፡፡ አብይና ኢሳያስ ለጎንዮሽ ውጋት የሚመዙት ካርድ እንደማይቸገሩ ለማሳየት ጥረት እያደረጉ ነው፡፡

 

ኦነግ ሸኔ በድርድር፣ ፋኖን በሰፈር ሽምግልና ለመደለል ጥረት ያደረገው መንግሥት እጅ ሲያጥረው፣ የእነ  ጃል መሮና ዘመነ ካሴ ጀምበር ወደ ኤርትራ በርሃ እያኮበኮበች ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በኢትዮጵያዊነት ቃላት ሸንግለውና አባብለው ከኤርትራ በርሃ ያስገቧቸው የትላንቶቹ ኦነግና ግንቦት ሰባት፣ ነጻ አውጭ ሆነው ለአራት ኪሎ ወንበር እየተናነቋቸው ነው፡፡

ጠቅላዮ ሰባተኛ ንጉስ ነኝ ያሉትን ቃላቸውን ጠብቀው በሥልጣኔ ከመጣችሁ ወይ ፍንክች ማለታቸው፣ ከኤርትራው ሳህል በርሃ እስከ አዲስ አበባ አፍንጫ ሥር አዲስ አቢዮን እያቀጣጠለ ይመስላል፡፡

አብይ እረሳቸው እንደሚሉት እርካብና መንበሩን በተቆጠጡ ማግስት፣ ከኤርትራ በርሃ ያመጧቸው እነ ዘመነ ካሴና ጃል መሮን ካለጠፋሁ ሰላም የለኝም ብለው ጦር ካዘመቱ ሰነባብተዋል፡፡

የኦሮሞው ነጻነት ሰራዊትና የአማራው ፋኖም መቶሺዎችን አሰልፈው ተክደናል ያሉትን መሻት ለማስመለስ ዙሪያ ገባውን ወጥረዋል፡፡ ጃል መሮ ከኬኒያ እስከ ታንዛኒያ ለድርድር ቢጋበዝም፣ እነ ዘመነ ደግሞ በሰፈር ሽምግልና ወደ ቤታችሁ ግቡ የተባሉ ቢባሉም ሁለቱም አሻፈረኝ ብለዋል፡፡

የእነ ጃል መሮና ዘመነ ካሴ የድርድርም ይሁን የሰፈር ሸምግልና አለመቀበል እና የአብይ በሥልጣኔ አትምጡ፣ በቀይ ባህር አትምጡብኝ ላሉት የቀጠናው የሽምቅ አለቃ ብስራት ሆናል፡፡

“ውረድ እንውደረጉ” ከኤርትራ ሳህል በርሃ እሰከ ጎጃም ጫካ፣ ከወለጋ የእነ ጃል መሮ መከተሚያ እስከ ወልቃይት ሁመራ በርሃ እየተፋጠነ ይመስላል፡፡

አብይም ይሄንኑ ከመንግድ ለማስቀረት የጦር መኮንኖቻቸውን በምድር በሰላማይ ከበባውን እዲያጠናክሩ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ከጀነራሎቻቸው አንደበት ተሰምቷል፡፡ ለአስመራውን የሽምቅ አለቃ የመልስ ምት “ብርጌድ ነሃመዶም” በኢትዮጵያ ተበስሯል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የሚፋለሙትን ኦነግ ሸኔንና ፋኖን የውጭ ኃይሎች ጃዝ የሚሏቸው ናቸው በማለት ኤርትራን ይወርፋል፡፡ የአስመራው መንግሥት ደግሞ ወዲህ ብርጌድ ንሃመዶምን በመደገፍ ወዲያ ደግሞ በቀይ ባህር ሰበሰብ ሉአላዊነቴ የሚፈታተን ትንኮሳ እያቃጨለብን ነው ይላል፡፡

“አስታጥቀህና አደራጅተው ከላክብኝ እኔም እልክብሃለሁ” የሚለውን ቋንቋ እየተቀኙ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ መሳሪያ ሆነው የሚያገለግሉት የኤርትራ ቤተኞቹ የኢትዮጵያ ታጣቂ ኃይሎችና በኢትዮጵያ መቀመጫ የተሰጠው ስደተኛው የአስመራው  ተቀናቃኝ ብርጌድ ንሃመዶም ናቸው፡፡

አብይና ኢሳያስ ፊት ለፊት ከመግጠም ይልቅ የሚቀናቀኗቸው ኃይሎችን እስር በእርስ ለመላላክ ወደ ኋላ የሚሉ አይመስሉም፡፡ ኢሳያስ ወትሮውንም ሸማቂዎችን አስታጥቀው መላክ ያውቁበታል፡፡ አብይም ቢሆኑ ዕድሉን ከገጠማቸው ይሄንኑ መንገድ ላይከተሉ የሚችሉበት ሁኔታ ይኖራል ተብሎ አይገመትም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ሥልጣን እንደመጡ “ኑ ወደቤታችሁ ግቡ” ብለው የጋበዟቸው የታጠቁ ኃይሎ ባልጠበቁት ሁኔታ፣ ፍርጠመው ተፋላሚዎቻቸው ሆነው ብቅ ማለታቸውን አልተቀበሉም፡፡

ለዚህም በየተራ ትጥቅ ለማፍታትም ይሁን ለመደምሰስ በኦሮሚያ ክልል አምስት ዓመት ገደማ፣ በአማራ ክልል ደግሞ አንድ ዓመት ገደማ ተዋገተዋል፡፡ ዓመታት የዘለቀውም ይሁን ወራት የዘለቀው ውጊያ በኃይል የሚቋጭ ባለመሆኑ፣ ላልሰመረ ድርድርምና ሽምግልና በቅቷል፡፡

በይፋዊ ድርድር የተሞከረው የኦነግ ሸኔ ኃይል ወደ ሰላም የማምጣት ጥረት፣ ለመንግሥት እረፍትም ተጨማሪ ኃይለም ይሆናል ተብሎ ነበር፡፡ ይሁን እንጅ ነገሩ ከታሰበው በተቃራኒ ሆኖ ጃል መሮም በሄድክበት ወደ ለመድከር ኤርትራ በርሃ ግባ ተብሏል፡፡

የእነ ጃል መሮ ድርድር ተሳክቶ ቢሆን፣ መንግሥት በአማራ ክልል ፋኖን ለማዳከም ተጨማሪ ጉልበት ያገኛል ወይም ቀጣዩ ድርድር ይሆናል ተብሎ ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ የኦሮሚያውም ይሁን የአማራ ክልሉ ታጣቂ ኃይል ትግል በኋል ሊቋጭ አልቻለም፡፡

ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት ታጣቂ ኃይሎቹ መሻታችንን መንግሥት ሆነን እናስፈጽማለን ሲሉ፣ መንግሥት ደግሞ በሥልጣን ከመጣችሁ እየተዋጋን እንቀጥላታለን እንጅ አታሰቡት ብሏል፡፡

በድርድርም ይሁን በሸምግልና ይሄን የመንግሥትን አቋም ያረጋገጡት ታጣቂ ኃይሎች፣ የአብይን መንግሥት ለመገርሰስ ከኤርትራ በኩል የሚያገኙት ድጋፍ ካለ ሳያቅሟሙ ከመጠቀም ወደ ኋላ አይሉም፡፡

ኦነግ ሸኔና ፋኖ ምንም እንኳን አሁን ላይ ቀላል የማይባል ኃይል በአገር ውስጥ ቢያሰልፉም፣ አርሷቸው ከኤርትራው ኦነግና ግንቦት ሰባት ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የኢሳያስና አብ ግንኙነትን መሻከር ተከትሎ ሊጎለብት የሚችል እንደሆነ ቀጠኛዊ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡

ሲያሻት የቀጠናውን መንግሥታት ወታደሮችን አሰልጥና ማሰልጠንና ተቃዋሚዎችን አስታጥቆ ማተራመስ የምታዉቅበት ኤርትራ፣ በእነ ጃል መሮንና ዘመነ ካሴን በኩል አብይን ለመውጋት የማትጠቀምበት ምክንያት አይኖርም፡፡

በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ደግሞ የኤርትራውን ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈርቂን ተቀነቃኝ “ብርጌድ ንሃመዶም”ን ለማስታጠቅ አሜን ብሎ ከመቀበል ወደ ኋላ እንማይል አስመስክሯል እየተባለ ነው፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው አብይና ኢሳያ በተቀያየ  ማግስት ብርጌድ ንሃመዶም አዲስግራት ላይ መመስረቱን አቶ ጌታቸው ረዳ አስተዳደር ማብሰሩ ነው፡፡

መንግሥት ከፋኖም ጋር ይሁን ከኦሮሚ ነጻነት ሰራዊት ጋር በሥልጣን ጉዳይ ፈጽሞ ሊደራደር እንማይችል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡ እንደሳቸው ገለጻ የታጠቁ ኃይሎች መንግሥትብ በክላሽ ተዋግተው አይጥሉም የሚል ነው፡፡

ጠቅላዩ እንዳሉት ፋኖም ይሁን ኦነግ ሸኔ በአጭር ጊዜ መንግሥትን በኃይል አሸንፈው ሥልጣን የሚቆጠጠሩበት ዕድል ላይኖር ይችላል፡፡ ወታደራዊ ተንታኞች እንደሚሉት ይነስም ይብዛም ሕዝባዊ ድጋፍ ያላቸው የታጠቁ ኃይሎች፣ መንግሥትን ማሸነፍ አይችሉም ማለት ይሸነፋሉ ማለት አይደለም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለው የመንግሥትና የታጠቁ ኃይሎች ፍልሚ በሸናፊና ተሸናፊ የሚቋጭ እንዳልሆነ ብዙዎች ይሞግታሉ፡፡ ይህ ማለት ተፋላሚ ኃይሎቹና መንግሥት ካልተደራደሩ ለዓመታት እየተዋጉ ይቀጠላሉ እንደማለት ነው፡፡

አሁን ያሉት አዝማሚያዎች የሚያመላክቱትም ይህንኑ ነው የሚሉ ምልከታዎች ከዚህም ከዚያም እየተሰሙ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይም በቅርቡ በፓርላማ ባሰሙት ንግግር፣ የአገሪቱን 10 ቢሊዮን ዶላር የፕሮጀክት ካሚታል ሊዋጉበት እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

ወዲህ ደግሞ የኢትዮጵያ ደንብር ቀይ ባህር ነበር መልሼ አመጣዋለሁ የሚለው የጠቅላዩ አጀንዳ፣ ኤርትራን እንዳስደነገጠ በይፋ ታይቷል፡፡  ቀይ ባህር የኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው ያሉት አብይ፣ ወደ ቀይ ባህር ለመጠጋት ሁሉም ይተባበር ቢሉም፣ የታጠቁ ኃይሎች  ቀይ ባህር ጉዳያችን አይደለም ብለዋል፡፡

ይህ አይነቱ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አካሄድ በድርድር የሚፈልጉትን ላለገኙት ታጣቂ ኃይሎችና ስጋት ለገባት ኤርትራ ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡ የታጣቁ ኃይሎች ለአብይ መንግሥት ውጋት ለአስመራው መግሥት ደግሞ እስትንፋስ ሆነው ሊመጡ ይችላሉ፡፡

የኤርትራ በርሃዎችን ምሸግ አድርገው ለዓማታት ጫካ ቤቴ ብለው የከረሙት የኦነግ ሸኔ መሪው ጃል መሮ እና የቀድሞው ግንቦት 7 ታጋይ የአሁኑ የፋኖ መሪ ዘመነ ካሴ መረብ ከአገር ቤት ኤርትራን ሊዘረጋ የሚችለበት ዕድልም ይሰፋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒትር አብይ አህመድና የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈርቂ ጸብ ለኦነግ ሸኔና ለፋኖ ብረታት ሆኖ የሚመጣበት ዕድልም ሰፊ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ ከወዲሁ የሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች የነፍስ አባት ኢሳያስ አፈርቂ ናቸው የሚሉ ድምጾችም ከመንግሥት ደጋፊ አክቲቪስቶች በኩል ተሰምቷል፡፡

በተለይ ፋኖ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ጠንካራ ጥምረት ሊፈጥር እንደሚችል በስፋት ሲነገር ይደመጣል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ኤርትራ ላይ የሚሰለጥን የፋኖ ኃይል እንዳለ ይነገራል፡፡ ከተበተነው የቀድሞው የአማራ ክልል ልዩ ኃይል መካከል በሁመራ በኩል  ወደ ኤርትራ የገባ እንዳለም ይነገራል፡፡

ከኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላቸው የፖለቲካ ሰዎችም፣ የአብይ አካሄድ አላማረንም ብለው የፋኖ ደጋፊ ሆነው ኮብልለዋል፡፡ የከሰመውን ኢሕአዴግን ለመፋለም የተከተሉትን መንገድ ኤርትራን ተገን አድርገው በብልጽናው መንግሥት ላይም እንደሚደግሙት በይፋ ተናግረዋል፡፡

እን አንዳርጋቸው ጽጌ ያሉ የአብይና ኢሳያስ ግንኙነት መረብ ነን የሚሊ ፖለቲከኞች፣ ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡ አሁን ላይ ለሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ዕድል የለም የሚሉ አካላት የኃይል አማራጮችን መደገፍ ምርጫቸው አደርገዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የለውጭ መንግሥት ተሸደናል ያሉ አካላት ዲያስፐራውን ጨምሮ፣ ሚሊዮን ዶላሮችን ለታጠቁ ኃይሎች እያቀበለ ነው፡፡ በአንጻሩ በተለይ ዲያስፖራው በመንግሥት ላይ የውጭ ምንዛሬ ማዕቀቦችና የዲፕሎማሲ ጫናዎችን ለመፍጥ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡

በዚህ ውስጥ ኤርትራዊያንን ጨምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚቃወሙና በተለይ ፋኖን የሚደግፉ አካሄዶች በግልጽ እየታዩ ነው፡፡ በተለይ የኢሳያስ መንግሥትና ፋኖ በአብይ መንግሥት ተከድተዋል የሚለው ሀሳብ ከሁለቱ ኃይሎች ጥምረት በር ከፋች ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

መንግሥት በሰሜኑ ጦርነት ወቅት አጀግኖ ከጎኑ አሰልፎ ሲያዋጋው የነበረውን ፋኖ በጠላትነት መፈጁ እና ከኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነት ማበላሸቱ አዲስ አሰላለፍ እንዲፈጠር እድል ፈጥሯል፡፡

ቀደም ሲል ሁለቱም ኃይሎች የመንግሥት አጋር ቢሆኑም፣ አሁን ላይ ሆድና ጀርባ ሆነዋል፡፡ ይህ ማለት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ለመተባበር የጋራ ተከጅነትና የጋራ ጠላት አገኙ እንደመላት ነው፡፡

ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ፋኖና ኤርትራ በወዳጅነት እየተሻሹ ነው የሚለውን ጭምጭምታ በገደምዳሜ አረጋግጧል፡፡ በእነ ዳቆን ዳንኤል ክብረት በኩል ጋላሚ የሚል ሰም የወጣላት ኤርትራ፣ ከፋኖ ጋር ለመተባበር ወደ ኋላ እንደማትል ምልክቶችን አሳይታለች፡፡

የኤርትራ መንግሥት የፕሮፖጋንዳ ክንፍ የሆኑ አክቲቪስቶች የሚያንጸባርቋቸው አቋሞች ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡ የአብይ መንግሥት ለክፉ ቀን ተጠቅሞ ከድቶናል የሚሉት እነዚህ አካላት ፋኖን በግልጽ ደግፈው መቆማቸውን አስመስክረዋል፡፡

የፋኖ ኃይሎች በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እርስ በእርስ መዋጋት ትተን ቀይ ባህርን በጋራ እናምጣ የሚለውን ሀሳብ፣ ጉዳያችን አይደለም ብለዋል፡፡ እንደውም ትኩረታችን መንግሥትን መገርሰስ እንጂ ከኤርትራ ጋር መጋጨት አይደለም ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

ኤርትራንና ፋኖን በአንድ ጎራ ያሰለፈው የህወሓትና የመንግሥት ስምምነትና የወልቃይት ጉዳይ ሌላኛው ትኩሳት ነው፡፡ እነ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ወልቃይት ከእጃችን አይወጣም የሚለው አቋማቸው ከመንግሥት ውሳኔ ጋር ተጋጭቷል፡፡

በኤርትራ በኩል ደግሞ ወልቃይት በአማራ እጅ ቢዘልቅ ይሻለኛል የሚሉ አቋም እንደሚኖራት ይገመታል፡፡ ይህ ማለት አንዱ የፋኖ መታገያ የሆነው የማንነትና ወሰን ጉዳይ ሌላኛው የጥምርት ምክንያት ሆኖ ይመጣል፡፡

ምናልባትም እነ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ የወልቃይት ዘብ ብለው ያሰታጠቁት ኃይል ወልቃይት በህዝበ ውሳኔ ይዳኝ የሚለው ቁርጥ የሆነ ዕለት ወደ ኤርትራ ሊተም ይችላል፡፡ ወልቃይት ላይ ያለው ኃይል ወልቃይትን በእጅ እንደያዘ ካልጸናለት ፋኖነቱን መግለጹ አይቀሬ እንደሆነም ብዙዎች ይናገራሉ፡፡

ፋኖ ለትግል ምክንያት አደርጎ ከሚያቀርባቸው ዋና ዋና ጥያቄዎች መካከል እንደ ወልቃይት ያሉ የማንነት ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ወልቃይት ወደ ትግራይና አማራ ክልል የመካለሉ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ ወሳኝ የጎረቤት አገር ድንበር መሆኑ የውጭ እጅም አያጣውም፡፡

መንግሥት የታጠቁ ኃይሎችን በድርድር ወደ ሰላም መመለስ አለመቻሉና ከኤርትራ ጋር ሊጣመሩ የሚችሉበት እድል መስፋት፣ ኢትዮጵያ በመጭዎቹ ዓመታት በቀውስ ውስጥ እንዲትቀጥል በር ይከፍታል፡፡

መንግሥትም ሥልጣንኑን በኃይል ለመጣበት ኃይል ላለመሰጠት የታጠቁ ኃይሎችም መንግሥትን ለመገርሰስ በሚያደርጉት ትግል፣ የለየለት የእርስ በእርስ ብጥብጥ ሊያስከትል እንደሚችልም ተንታኞች እየገለጹ ነው፡፡

የአማራ እና ኦሮሚያ ክልሉ ውጊያ በድርድር ካልተቋጨና በሂድ አካሄዱ ቀጥሎ እንደ አቀጣጣይ ሁነቶች ከተፈጠሩበት፣ ቀጠናውን ወደ ጦርነት ሊያስገባ እንደሚችል የጂኦፖሊክስ ተንታኞች እየጻፉ ው፡፡

የኢትዮጵያን የውስጥ ቀውስ በቀጠናው ውጥረት ከፈጠረው የቀይ ባህር አጀንዳ ጋር ያገናኙት ትንታኞች፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ የቀጠናውን እጣ ፈንታ የሚበይን ነው እያሉ ነው፡፡ እንደ አሜሪካ ያሉ ኃያላን አገራትም የቀጠናውን ሰላም ለመጠበቅ መንግሥት ከታጠቁ ኃይሎች ጋር እንድደራደር ግፊት እያደረጉ ነው፡፡

መንግሥት በውጭ ግፊትም ይሁን ለራሱ ብሎ ለፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ከተደራደረ፣ ከዚህም ከዚያም የታዩት ስጋቶች የማስቀረት እድል ይኖረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የራበውን ሰላምና የጠማውን ፍቅርም የሚያገኝበት በር ዝግ አይደለም፡፡

ሰላም ለሰው ልጆች ሁሉ!

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ኢትዮጵያን ማን ያሻግራት?

ዳግማዊ ትግራይ በአማራ ላይ!